ትምህርተ ሃይማኖት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት

“ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” ዕብ 11፡ 6

ሃይማኖት ”ሀይመነ” አመነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ማመን፤መታመን፤ ታማኒነት፤አመኔታ ማለት ነው።

  • ማመን ፦ማለት ከሁሉ በፊት የነበረ ፡ዓለምን ሰሳልፎ የሚኖር ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ ማንኛውንም ነገር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ያስገኘ፤ለእርሱ ግን አምጭ ፤አስገኝ፤ አሳላፊ የሌለው ፤ ምንም ምን የሚሳነው የሌለው ፤በአንድነት በሦስትነት ጸንቶ ያለ ፤ሁሉን ቻይ የማይለወጥ አምላክ መኖሩን ማመን ነው።
  • መታመን፦ ማለት በልብ /በረቂቅ አእምሮ/ ያመኑትን በአንደበት መመስከር መናገር፤ማመስገን ማምለክ ፤መስገድ ፤መገዛት ’ለቃሉ ታዛዥ ፤ለመንግስቱ ተገዥ መሆን በስራ ሁሉ መግለጥ ማለት ነው። /ሮሜ 10፡9/
  • ተአማኒነት፦ማለት ይደረግልኛል፤ ይሆንልኛል፡ይፈፀምልኛል ብሎ በፍፁም ልብ በእግዚአብሔር ላይ ተአማኒነት ማድረግ ነው።
  • አመኔታ፦ ተአማኒነት ከሚለው ጋር በትርጉም ተወራራሽነት አለው።

ይኸውም ሃይማኖት ማለት ቅድመ ዓለም የነበረ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ፈጥሮም የሚገዛ ማዕከለ አለም ያለ ፤ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ምንም የሚሳነው የሌለ ለእርሱ ግን አምጭ ፤አስገኝ፤ አሳላፊ የሌለው በአንድነት፤ በሦስትነት የሚመለክ ዘለዓለማዊ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ማመን ነው። /ዕብ፡11 1-40/

ሃይማኖት ማለት ፍጡር ፈጣሪውን ለማወቅ ባሰበ ጊዜ ፤እንደመላእክት በአእምሮ ጠባይዓዊ ፤ እንደነ አብርሃም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ እንደነብያትና እንደ ሐዋርያት ፊቱን አይቶ ቃል በቃል ተነጋግሮ ፤እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በተአምራት ተገልጾለት ተመልሶ እንደሌሎች ምእመናንም በአእምሮ መጽሐፋዊና በተስፋ አረጋግጦ አምላክ እንዳለ የሚያምኑበት እውነተኛ ትምህርት ነው እንጂ እንደ እቃ በእጅ የሚጨበጥና የሚዳሰስ እንደልብስም የሚለበስ ፤እንደ መብልና መጠጥም የሚቀመስ አይደለም። ዕብ 11

ስለ እግዚአብሔር በመጽሀፍ ቅዱስ የተነገረውን ሁሉ በልባችን የምናምንበት ፤በአፋችን የምንታመንበት መግለጫ ሃይማኖት ነው። ሃይማኖት ማለት በአይን የማይታየውን በእጅ የማይዳሰሰውን የልዑል እግዚአብሔርን ነገር ይህ እንዴት ይሆናል? ማለት ሳይኖር በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል ብሎ በሙሉ ልብ ማመን ፤ ይህንንም በአፍም በመጽሐፍም መመስከር ነው።

ይቀጥላል……..

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አርአያ ቅዱሳን

አርአያ ቅዱሳን

ቅዱስ ቀሌምንጦስ /91-100/

ይህ ታላቅ አባት በሮም ተወልዶ በዘመነ ሐዋርያት ከቅዱስ ጴጥሮስ ማዕረገ ክህነት የተቀበለና የእርሱ ደቀመዝሙር የነበረ ሲሆን ስጋዊ ትምህርቱን በዚያው በሮም ያጠናቀቀ ምሁር ነበር። በቅዱስ ጴጥሮስ ሲመት የሮም ኤጲስ ቆጶስነት ተሰጥቶት ከሰባ ሁለቱ (72) አርድእት አንዱና የክርስትናን ትምህርት በፈሊጥ ካስተማሩትና የቤተክርስቲያን ቀኖናን በጽሁፍ ካወረሱን ታላላቅ ሊቃውንት አባቶች ከዋነኞቹ አንዱ ነው።

ቅዱስ ቀሌሜንጦስን ቅዱስን ጳውሎስ በፊሊ 4፡3 ላይ የጠቀሰውና ለእርሱም በማስተማር ጊዜ ረዳቱ የነበረ መሆኑ ይነገርለታል። የቆሮንጦስ ሰዎች (ምዕመናንና ምዕመናት) ሁከትና ረብሻ ስለነበረባቸው 1ኛ ቆሮ 1፤10-17 ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰጣቸው ምክርና ተግሳጽ በተጨማሪ ይህ ታላቅ አባት በ96 ዓ.ም ቦታው ላይ በመገኘት ሰላም እንዲሰፍን ምክር ከሰጠ በኃላ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ላይ የተመሰረቱ ሁለት መልእክታትን ጽፎ በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ለምዕመናን እንዲነበብላቸው አድርጓል።

የቆሮንቶስ ጳጳስ አቡነ ዲዮናሲዮስ 170 ዓ.ም ለሮም ፓፓ ለስቴር የላከው ደብዳቤ በዚሁ አባት የተጻፈ ነው። የመጀመሪያ መልዕክት በበዓላትና በሰንበት ቀን በቤተክርስቲያን ለሚሰበሰቡ በየጊዜው በመነበብ ላይ ይገኛል።

የቅዱስ ቀሌሜንጦስ መልዕክታት ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም መቀመጥ ስለቅዱስ ጳውሎስ ማስተማርና ወደ እስፓኝ ስላደረገው ጉዞ እንዲሁም የሁለቱ ሊቃነ ሐዋርያት በኔሮን ቄሳር ዘመን የተቀበሉትን ሰማዕትነት የሚያብራራ ሲሆን ለቤተ ክርስቲያንም ስለ ማዕረገ ክህነት ስለ ምዕመናን ፤ ስለንስሃ ፤ ስለትንሳኤ ሙታን የተመለከቱ ነጥቦችን ከትቦ አቆይቷል።

ቅዱስ ቀሌሜንጦስ የቅዱስ ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የቀዱስ ጳውሎስ የትምህርት ፈሊጥ አድናቂ የነበረ ሲሆን በመጽሐፉም ከቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት የሮሜን የቆሮንቶስንና የኤፌሶንን መልእክት እየጠቀሰ መጽሐፍትን በማብራራትና የስነ-ምግባራትን ህግጋት በማተኮር የፃፈ በመሆኑ በቤተክርስቲያናችን መጽሐፉ ከሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት እንደ አንዱ የሚቆጠር ነው።

ሐዋርያት ፍጻሜያቸው በሰማዕትነት የሚጠናቀቅ፤ ተጋድሏቸው በትሩፋት የተገነባና ክብራቸው የደም ሐውልት የሰራ እንደመሆኑ መጠን እርሱም ተረኛ ሆኖ ማስተማሩ እንደወንጀል ተቆጥሮ በንጉስ ትራጃን ዘሮም ዘመነ መንግስት በ 100 ዓ.ም በስደት ሲንገላታ ከቆየ በኃላ በፅኑ እስር ቆይቶ አንገቱ ላይ በገመድ /በመልሕቅ/ ታስሮ ጥቁር ባህር ውስጥ ተጥሎ አርፏል።የአርድእቱ በረከትን ያሳድርብን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግ

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማለት ለመረዳት እንዲመቸን እያንዳንዳቸውን ቃላት ለመተንተን እንሞክራለን፡

  • ክርስቲያን ማለት የክርስትና ሃይማኖት መሥራችና ባለቤት በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አምላክነትና አዳኝነት አምኖ የተጠመቀና የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚጠራበት በክርስቶስ የወረስነው ስም ነው፡፡  ይህም ስም ምንም እንኳን የሚጠሩበት ሁሉ በነጻ የተቸራቸው ስጦታ ቢሆንም የስሙ ባለቤት ክርስቶስ ግን ይህንን ስም ለሚሹ ሁሉ ለመስጠት የከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት በፊደል ድርደራና በቃላት ቅንብር መግለጽ አይቻልም፡፡ ‹‹ስለ ጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ሊገባ ይችላል ስለ ቸር ሰውም የሚሞት ምናልባት ሊገኝ ይችል ይሆናል፡፡›› ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና በዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፡፡ ሮሜ 3፥5-7

ይህ ክርስትና ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት በመኖር ቅድስና ክብርን ለማግኘት የተዘጋጀ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሚጠሩበት ስም ነው፡፡ ‹‹ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው›› ዮሐ. 1፥12

‹‹ክርስትና›› ሰዎች በፍቅረ እግዚአብሔር ተስበው ፈጣሪያቸውን አውቀው በነፍሳቸውም እረፍትን ሽተው በሕጉና በትዕዛዙ ጸንተው ለመኖር ሲሉ ራሳቸውን ከዓለም ፈቃድ ነጥለውና ሁለንተናቸውን ለእርሱ የሰጡ ሆነው የሚኖሩበት ሕይወት ነው፡፡ ‹‹ዓለምና ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘለዓለም ይኖራል›› 1ዮሐ. 2፥17

  • ሥነ ማለት ሠናየ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ማማር’ መዋብ ማለት ነው፡፡
  • ምግባር ማለት ገብረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ተግባር ክንውን ማለት ነው፡፡
  • ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማለት የክርስቲያን መልካም ሥራ ያማረ ተግባር የተዋበ ክንውን ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ያመነ ሰው የሚሠራው መልካም/ያማረ ተግባር ማለት ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሕገ ልቦና

ሕገ ልቦና ማለት እግዚአብሔር አምላክ በልቦናቸው ሕግ እየደነገገላቸው ምንም የተጻፈ ሕግ ያልኖራቸው ወይም በቃል ሳይነግሯቸው መልካም የሆነውን በልቦናቸው አውቀው የሚሠሩት ሕግ ነው፡፡

ይህ ሕግ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ያለው 2256 ድረስ ነው፡፡ በሕገ ልቦና የነበሩ አባቶች መልካም ሥራ ይሠሩ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ጻድቁ አብርሃም ከመልካም ሥራዎቹን ውስጥ ቤቱ እንግዶችን እየተቀበለ በፍጹም ትሕትና እግራቸው እያጠበ ምግብን መጠጡን እያቀረበ ያስተናግድ እንደ ነበር ተገልፃል፡፡ ‹‹ እግራችሁን የምትታጠቡበት ውኃ እስካመጣላችሁ ድረስ በዚህ ጥላ ሥር እርፍ በሉ . . . ጥቂት ምግብ ይምጣላችሁ እንዳስተናግዳቸሁ ፍቀድልኝ›› ዘፍ. 18፥4  ይህንንም ሥርዓት የአብርሀናም ዘውድ የነበረው ሎጥ እንደሚፈጸም ዘፍ. 19፥1 ስር ተገልፀዋል፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግብር በሕገ ኦሪት

ኦሪት ማለት የሱርስት ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ብርሃን ማለት ነው፡፡ ‹‹ ከዘመነ ኦሪት ከሙሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ጊዜ ድረስ የነበረ ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ የተፃፈ ሕግ ሲሆን እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን ያስተላለፈው ሕግ ነው እግዚአብሔር ለምን ይህን ሕግ ሰጣቸው ቢሉ? እስራኤላውያን በአረማውያን መካከል በሚኖሩበት ጊዜ እንዲለይበት እንዲቀደሱበት እራሳቸውንም ልጆቻቸውንም ከኃጢአት እንዲታቀቡበት በጽድቅ ላይ ጽድቅ በትሩፋት ላይ ትሩፋት የሚያገኙበት እራሳቸውን ከአሕዛብ ይለዩበት ዘንድ የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ በዚህ ኦሪት መጽሐፍ ላይ እስራኤላውያን በማኅበራዊ አኗኗራቸው ጊዜ እንዲፈጽሙ ከተነገራቸው ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው፡፡

  • በአለባበሳቸው ዘዳ. 22፥5 ዘዳ. 22፥11-12
  •  በአመጋገባቸው ዘዳ. 14፥3-21
  •  የለቅሶ ልማድ ዘዳ. 14፥1-2

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሕገ ወንጌል

ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የምንመራበት ሕግ ነው፡፡ የሕገ ወንጌል መሥራች ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ሥርዓቶች በሐዲስ ኪዳን ሥርዓቶች እየለወጠና እየፈጸመ በተግባር ያሳየን ያስተማረን አምላካችን ነው፡፡‹‹ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ›› በማለት በሁሉ እርሱን አብነት በማድረግ እንዲገባን የነገረን፡፡ ማቴ. 11፥29

ወስብሐት ለእግዚአብሔር