ትምህርተ ሃይማኖት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት

“ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” ዕብ 11፡ 6

ሃይማኖት ”ሀይመነ” አመነ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ማመን፤መታመን፤ ታማኒነት፤አመኔታ ማለት ነው።

  • ማመን ፦ማለት ከሁሉ በፊት የነበረ ፡ዓለምን ሰሳልፎ የሚኖር ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ ማንኛውንም ነገር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ያስገኘ፤ለእርሱ ግን አምጭ ፤አስገኝ፤ አሳላፊ የሌለው ፤ ምንም ምን የሚሳነው የሌለው ፤በአንድነት በሦስትነት ጸንቶ ያለ ፤ሁሉን ቻይ የማይለወጥ አምላክ መኖሩን ማመን ነው።
  • መታመን፦ ማለት በልብ /በረቂቅ አእምሮ/ ያመኑትን በአንደበት መመስከር መናገር፤ማመስገን ማምለክ ፤መስገድ ፤መገዛት ’ለቃሉ ታዛዥ ፤ለመንግስቱ ተገዥ መሆን በስራ ሁሉ መግለጥ ማለት ነው። /ሮሜ 10፡9/
  • ተአማኒነት፦ማለት ይደረግልኛል፤ ይሆንልኛል፡ይፈፀምልኛል ብሎ በፍፁም ልብ በእግዚአብሔር ላይ ተአማኒነት ማድረግ ነው።
  • አመኔታ፦ ተአማኒነት ከሚለው ጋር በትርጉም ተወራራሽነት አለው።

ይኸውም ሃይማኖት ማለት ቅድመ ዓለም የነበረ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ፈጥሮም የሚገዛ ማዕከለ አለም ያለ ፤ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ምንም የሚሳነው የሌለ ለእርሱ ግን አምጭ ፤አስገኝ፤ አሳላፊ የሌለው በአንድነት፤ በሦስትነት የሚመለክ ዘለዓለማዊ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ማመን ነው። /ዕብ፡11 1-40/

ሃይማኖት ማለት ፍጡር ፈጣሪውን ለማወቅ ባሰበ ጊዜ ፤እንደመላእክት በአእምሮ ጠባይዓዊ ፤ እንደነ አብርሃም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ እንደነብያትና እንደ ሐዋርያት ፊቱን አይቶ ቃል በቃል ተነጋግሮ ፤እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በተአምራት ተገልጾለት ተመልሶ እንደሌሎች ምእመናንም በአእምሮ መጽሐፋዊና በተስፋ አረጋግጦ አምላክ እንዳለ የሚያምኑበት እውነተኛ ትምህርት ነው እንጂ እንደ እቃ በእጅ የሚጨበጥና የሚዳሰስ እንደልብስም የሚለበስ ፤እንደ መብልና መጠጥም የሚቀመስ አይደለም። ዕብ 11

ስለ እግዚአብሔር በመጽሀፍ ቅዱስ የተነገረውን ሁሉ በልባችን የምናምንበት ፤በአፋችን የምንታመንበት መግለጫ ሃይማኖት ነው። ሃይማኖት ማለት በአይን የማይታየውን በእጅ የማይዳሰሰውን የልዑል እግዚአብሔርን ነገር ይህ እንዴት ይሆናል? ማለት ሳይኖር በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል ብሎ በሙሉ ልብ ማመን ፤ ይህንንም በአፍም በመጽሐፍም መመስከር ነው።

ይቀጥላል……..

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *